ከ20 ሺሕ በላይ አባወራዎችን ሥጋት ላይ የሚጥል የጎርፍ አደጋ በአዲስ አበባ ሊከሰት ይችላል

0

በመጪዎቹ የክረምት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ 169 ቦታዎች ለጎርፍ ሥጋት እንደሚጋለጡ፣ የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በአደጋው በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ከ30 በላይ ወረዳዎች ተጋላጭ እንደሆኑ፣ 20,955 አባወራዎችም የጉዳት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለሪፖርተር የገለጹት፣ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ናቸው፡፡

900 በላይ ተቋማትም ለጎርፍ አደጋው ተጋላጭ እንደሆኑና ተገቢው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ካልተከናወነ፣ 4.3 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት ሊወድም እንደሚችል አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት የታየባቸው በአቃቂ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 3፣ 8፣ 2፣ 4)፣ በየካ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 9፣ 7፣ 12፣ 5፣ 11፣ 2፣ 3፣ 4)፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 13፣ 1፣ 9፣ 6)፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 8፣ 5)፣ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 7)፣ በኮልፌ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 11፣ 5፣ 6፣ 10)፣ በልደታ ክፍለ (ወረዳ 3፣ 5፣ 14፣ 8፣ 10)፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 4፣ 6፣ 3፣ 5፣ 7፣ 8፣ 9፣ 10)፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 6፣ 1፣ 2)፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ (ወረዳ 6፣ 7፣ 9 እና 10) እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በተጠቀሱት ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች ከ60 በላይ የሚሆኑ ሥፍራዎች በወንዝ ተፋሰስ ምክንያት ከፍተኛ ተጋላጭነት እንዳላቸው አቶ ንጋቱ ገዋጸዋል፡፡፡

በከተማዋ ከባድ የጎርፍ ችግር እንዳለበት በሚነገረው አቃቂ አካባቢ አምና በደረሰ የጎርፍ አደጋ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ያስታወሱት አቶ ንጋቱ፣ በዚህም ዓመት ዋናው ክረምት ከመግባቱ አስቀድሞ ከቀናት በፊት ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ አስረድተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ባለፈው ዓመት 2010 ዓ.ም. አቃቂ አካባቢ በተከሰቱ 55 የጎርፍ አደጋዎች ከ527 የሚበልጡ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ እስካሁን ድረስ በአካባቢው በሚገኙ የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ አምና በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች 33 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ተብሏል፡፡ እነዚህ ኮሚሽኑ በደሰው ሪፖርት በየቦታው ተገኝቶ ምላሽ የሰጠባቸው ብቻ እንጂ፣ በከተማዋ የተከሰቱትን አጠቃላይ የጎርፍ አደጋዎች ቁጥር አይወክሉም፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለተከሰቱ 423 አደጋዎችም ምላሽ መስጠቱ ታውቋል፡፡ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙ እንደሚያሳየው፣ 423 አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡ 299 ከእሳት፣ 124 ደግሞ ከጎርፍ፣ ከኤሌክትሪክ፣ ከግንባታ ሳይቶች ጋር የተያያዙ አደጋዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አደጋዎች 68 ሰዎች ሲሞቱ፣ 96 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡ 230 ሚሊዮን ብር ገደማ በሚገመት ንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱ፣ 90 በመቶ ለሚሆነው በንብረት ላይ ለደረሰው ውድመት መንስዔው የእሳት አደጋ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ደግሞ በአጠቃላይ 437 አደጋዎች መመዝገባቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 270 የእሳት፣ 167 ደግሞ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንደነበሩ አቶ ንጋቱ አስታውሰዋል፡፡ በተመሳሳይ በጀት ዓመት ውስጥ በደረሱት 437 አደጋዎች 65 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ 74 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ 183 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም አስረድተዋል፡፡

በሰዎች ላይ ለሚደርሱ አብዛኞቹ አደጋዎች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተቆፈሩ የተተው ሰፊፋ ጉድጓዶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ በወረዳ 1 ሃና ማርያም፣ በወረዳ 11 ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወርዳ 13 ቦሌ ቡልቡላ እንዲሁም ኤርፖርት ጀርባ በወረዳ 5 ሰሚት አካባቢ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የካ አባዶ አካባቢ፣ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ጨሬ መድኃኔዓለም አካባቢ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቻይና ካምፕ አካባቢ ተቆፍረው የተተው ሰፋፊ ጉድጓዶች ለብዙ አደጋዎች መንስዔ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በየዓመቱ በሚደርሱ የእሳት አደጋዎች እስከ አራት ሰዎች እንደሚሞቱ የሚናገሩት አቶ ንጋቱ አዲስ ከተማ፣ ቂርቆስ፣ አራዳና ንፋስ ስልክ ክፍላተ ከተሞች በተደጋጋሚ የእሳት አደጋዎች የሚመዘገቡባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ቤቶቹ የተገነቡባቸው ቁሶችና የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በቀላሉ ለእሳት አደጋ እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት አደጋዎች በጥንቃቄ ጉድለትና በቸልተኝነት የተከሰቱ መሆናቸውን፣ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ 4.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ውድመት ማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመት የወደመው 230 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ንብረት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ ዓለም ገና፣ ገላንና ጣፎ አካባቢ የደረሱትን አደጋዎች ድምር ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ እየደረሱ ያሉና ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

Source: The Reporter

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.