የሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ ”በሃገራት” ዝርዝር ሥር መካተት ሶማሊያውያንን አስቆጣ

0

በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድረ-ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ በሶማሊያውን ዘንድ ሌላ ቁጣን ቀስቀሰ።

ከሁለት ቀናት በፊት እንደወጣ የሚታመነው እና በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድረ-ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ያላትን ሃገራት ዝርዝር ያስቀምጣል። ታዲያ ሃገራት በሚለው ዝርዝር ሥር የሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ ሥም መስፈሩ ነው የውዝግቡ መነሻ።

የሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ በሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ግዛቶች ሲሆኑ ሁለቱም ዓለም አቀፍ እውቅናን ባያገኙም እራሳቸውን እንደ ነጻ ሃገር ይቆጥራሉ።

 

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ድረ-ገጽ ሁለቱን ግዛቶችን በሃገራት ዝርዝር ሥር ማካተቱ በርካታ ሶማሊያውያንን አስቆጥቷል። ከእነዚህም መካከል የቀድሞ ሚንስትር እና በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አብዲ አይኔት፤ ከቀናት በፊት የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር በአፍሪካ ካርታ ላይ የሰራውን ስህታት በማስታወስ ”የመጀመሪያው በስህተት ነው ካሉ፤ ይህንስ ምን ሊሉ ነው? የሶማሊያን እንድነት እና ሉዓላዊነት የመካድ አባዜ የሰነበተ ነው” ሲሉ ትዊተር ገጻቸው ላይ በሶማልኛ አስፍረዋል።

የቀድሞ የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር የሱፍ ጋራድ በበኩላቸው ”መንግሥታችን ስለካርታው ዝምታን እንደመረጠው ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝም ማለት የለበትም” ማለት ጽፈዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እና ፑንትላንድን እንደ አንድ የሶማሊያ ፌደራል ክልል እንጂ እንደ ሃገር እንደማትቆጥር አረጋግጠው በድረ-ገጹ ላይ የሰፈረው ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታደርግባቸው ስፍራዎች ዝርዝር እንጂ የሃገራት ዝርዝር አይደለም ብለዋል።

አቶ ነቢያት ይህን ይበሉ እንጂ በድረ-ገጹ ሶማሊላንድን እና ፑንትላንድን የተዘረዘሩት ሃገራት በሚለው ዝርዝር ስር ነው። አቶ ነቢያት የውጪ ጉዳይ ሚንሰቴር ድረ-ገጽ ላይ በርካታ ስህተቶች እንዳሉ አምነው ስህተቶቹን ለማረም እየሰራን ነው ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ ብቻ ነው ኤምባሲ ያላት የሚሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት፤ በሐርጌሳ (ሶማሊላንድ) እና በፑንትላንድ ጥቅሟን የምታስከብርበት ቆንፅላ ጄነራል ነው ያላት ብለዋል።

ማንኛውም ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያለው ሀገር ጥቅሙን የሚያስከብርበት ከኤምባሲ ባሻገር ተጨማሪ ጽህፈት ቤቶች መክፈት ይፈቀድለታል የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ ኢትዮጵያ በቻይና መዲና ቤይጂንግ ኤምባሲ እንዳላት አስታውሰው በአራት የቻይና ከተሞች ደግሞ ቆንፅላ ፅህፈት ቤቶች እንዳሉ ገልጠዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ታከብራለች ያሉት ቃል አቀባዩ ለዚህም ሶማሊያ ውስጥ ያለው አንድ ኤምባሲ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምታውቀው አንድ ሶማሊያን ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ሌሎቹ የፌደራል ክልሎች ናቸው በእነዚህ ክልሎች ቆንፅላ ጽህፈት ቤት አለን ማለት እንደ አገር ይታያሉ ማለት አይደለም ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እለት የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በድረ ገፁ ላይ ይዞት የወጣው የአፍሪካ ካርታ የኢትዮጵያ ካርታ ሙሉ በሙሉ ሶማሊያን አካትቶ ይዞ የሚያሳይ መሆኑ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወዲያው ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን በድረ-ገፁ ላይም በምትኩ የድርጅቱን አርማ አስፍሮ ነበር።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ትናንትና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይም ይህንን ያደረገው ማን እንደሆነ እንደሚጣራና እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጠዋል።

ይህ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ካርታ እንዲሁም ሁለቱ የሶማሊያ ግዛቶች ሃገራት በሚል ስር መዘርዘራቸው ጉዳይ በበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነታረኪያ ሆኖ ቀጥሏል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ራሷን እንደ ነጻ ሃገር ብታውጅም የትኛውም ሃገር እውቅና አልሰጣትም።

በተመሳሳይ መልኩ ፑንትላንድ እአአ 1998 ላይ ራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ብታውጅም የትኛም ሃገር እውቅና አልሰጣትም።

Source: BBC Amharic

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.