በጅግጅጋና አካባቢው በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተገለጸ

0

ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በአካባቢው በተፈጸመ የእሳት ቃጠሎ የወደሙት የኦርቶዶክስ የእምነት ተቋማት ግምት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን አስታወቀ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት እንደገለጸው ሃይማኖትን፣ ማንነትንና ቋንቋን መሠረት በማድረግ ለአምስት ቀናት በተፈጸሙ ግድያ፣ ቃጠሎና መፈናቀል ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውሷል፡፡ በእምነት ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት የተገለጸውን ያህል መሆኑንም፣ በክልሉ ያለው መርማሪ ቡድን ማሳወቁን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ክራውን የሚባል ሆቴል ሙሉ በሙሉ መቃጠሉንና የወደመው ንብረት ግምትም 42 ሚሊዮን ብር መሆኑ እንደታወቀ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ምርመራውን ለምን ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ፍርድ ቤቱ ጠይቆት መርማሪ ቡድኑ ምላሽ ሲሰጥ፣ የወንጀል ድርጊቱ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሲደርስ ነበር ብሏል፡፡ በተለይ የክልሉ ተወላጆች ሆነው የሥርዓቱ ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ ‹‹አሸባሪዎች›› እየተባሉ፣ ከ200 በላይ ዜጎች መገደላቸውንና ከአንድ ቤተሰብ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ከቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎችን ወደ ክልሉ ይዞ በመሄድ አስከሬኖችን ከጅምላ መቃብር በማውጣት የመለየት ሥራ ማከናወኑን መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ በሥርዓት እንዲቀበሩም ማድረጉንና ለማስረጃም ፎቶግራፍ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡ ከክልሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ 101 ገጽ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን በመቀበል ለትርጉም መስጠቱንም ገልጿል፡፡

የተገደሉት ሰዎች ቤተሰቦች በወቅቱ በመሸሻቸው የሟቾች ማንነትን መለየት ባለመቻሉ፣ ተጨማሪ የምርመራ ቡድን በማቋቋም ወደ ክልሉ ልኮ ቤተሰቦቻቸውን በማፈላለግ ላይ መሆኑንና ለትርጉም የሰጠውን ሰነድ ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ ምርምራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች ባቀረቡት ተቃውሞ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ እያቀረበ ያለው የምርመራ ሒደት ተመሳሳይ ከመሆኑ በተጨማሪ ምርመራውን ወደ ኋላ እየወሰደ ከ2004 ዓ.ም. መጀመሩ ተገቢ አይደለም፡፡ የወንጀል ድርጊቱ የጀመረው በ2004 ዓ.ም. ከሆነ አቶ አብዱራዛቅ ሳኒ በወቅቱ ተማሪ በመሆናቸው እንደማይመለከታቸው አስረድተዋል፡፡ ከመጀመርያው ክርክር ጀምሮ ምርመራው ተለይቶ እንዲቀርብ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ የክርክር ሒደቱ በተገቢውና በአግባቡ ለመከራከር እንዳስቸገራቸው ተናግረዋል፡፡

የወ/ሮ ረሃማ መሐመድ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በፌዴራል መጀመርያ ቅድመ ምርመራ ፍርድ ቤት ምስክርነት ተሰምቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን ማጠናቀቁን ተናግሮና ዓቃቤ ሕግም አብሮ ቀርቦ አንድ ሙሉ ቀን የፈጀ ምስክርነት መሰማቱን አስረድተው፣ ‹‹እንዴት እንደገና ሌላ ምርመራና ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ይጠየቃል?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ከተጠርጣሪነት ወደ ተከሳሽነት፣ እንደገና ወደ ተጠርጣሪነት መመላለሱ ምን ማለት እንደሆነ እንዳልገባቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱም ስለማይፈቅድ መዝገቡ ተዘግቶ ደንበኞቻቸው እንዲሰናበቱም ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተጠየቀው ጊዜ በቂ ስለመሆኑና አለመሆኑን መመዘን እንዳለበትም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ መዝገብ ተመልክቷል፡፡ በሰጠው ትዕዛዝም የመርማሪ ቡድኑ መዝገብ ሥራ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን እንደሚያሳይ አስታውቆ፣ ጉዳይ ውስብስብ መሆኑን ስለተገነዘበ የተጠየቀውን 14 ቀናት መፈቀዱን በመግለጽ ለኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Via The Reporter

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.