ኃይሌ ሪዞርት የጎንደሩን ላንድ ማርክ ሆቴል ተረከበ

0

በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ መስኮች ውስጥ የተሠማራው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ በሆቴል መስክ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት በዘረጋው ውጥን መሠረት ስድስተኛውን ሪዞርት ሆቴል በጎንደር ከተማ ሥራ ለማስጀመር መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በአምስት ዓመታት ውስጥ የሆቴሎችና ሪዞርቶቹን ቁጥር 20 ለማድረስ በያዘው ዕቅድ ዕቅድ መሠረት፣ በጎንደር ከተማ አስፈላጊውን የዝግጅት ሒደት አጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የሚጠባበቀው ላንድ ማርክ የተባለውን ሆቴል፣ በኃይሌ ሪዞርት ሥር እንዲተዳደር ለ15 ዓመታት በመከራየት ነው፡፡ ከላንድ ማርክ ጋር የተፈረመውን ስምምነት በማስመልከት አትሌት ኃይሌና የላንድ ማርክ ሆቴል ባለቤት አቶ ነጋ አዲሱ በሰጡት መግለጫ ወቅት አትሌት ኃይሌ እንደገለጸው፣ ጎንደር ስድስተኛ መዳረሻው ለመሆን የተመረጠችው በታሪካዊነቷና በቱሪስቶች መዳረሻነቷ ጭምር ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በጎንደር ያለው የሆቴል ሥራ አዋጭነትም ተጠንቶ ኃይሌ ሪዞርት እንዲከፈት መወሰኑን ኃይሌ አስታውቋል፡፡

ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከላንድ ማርክ ጋር የገባው ስምምነት በየአምስት ዓመቱ እየታደሰ ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ የኪራይ ውል ሲሆን፣ የሆቴሉ ነባር ስያሜም  ወደ ኃይሌ ሪዞርት ተቀይሮ ከኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ የማስፋፊያ ዕቅዱን ከሆቴል ግንባታ በተጨማሪ፣ በኪራይ ውል፣ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በመረከብ በስሙ የማስተዳደርና ስሙን ለሌሎች ሆቴሎችና ሪዞርቶች በመሸጥ ጭምር የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ የጎንደሩ ኃይሌ ሪዞርትም በዚሁ አግባብ በኪራይ የሚሠራበት እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል ባለቤት የአርክቴክቸር ምሩቁ አቶ ነጋ በበኩላቸው፣ በዕውቀታቸውና አቅማቸው የጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴልን እንደገነቡት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሆቴሉን ለማስተዳደር ራሱን የቻለ ሳይንስ የሚጠይቅ በመሆኑ ለዘርፉ ባለሙያዎች በመስጠት፣ ሆቴሉን ይበልጥ ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡንም ማሻሻል ተገቢ እንደሆነ በማመን ለኃይሌ ሪዞርት በኪራይ ለመስጠት እንደወሰኑ አስታውቀዋል፡፡

ኃይሌ ሪዞርትን ምርጫቸው ያደረጉትበትም ምክንያት በአገሪቱ በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶች አንዱ በመሆኑና ይዞ ከተነሳው ራዕይ አንፃር፣ ምርጫቸው እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡ ሆቴሉን ደረጃ በደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ለማሟላት እንደታቀደና በኃይሌ ሪዞርት ስም አገልግሎት እስከሚጀምርበት ድረስ ግን ሆቴሉ በሪዞርት ደረጃ አገልግሎት ለመስጠት በሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ተጨማሪ ግንባታዎችና ዕድሳት እንደሚደረግለት አትሌት ኃይሌ ገልጿል፡፡

እንደ ኃይሌ ገለጻ ሆቴሉን በሪዞርት ደረጃ ለማስተዳደር ከ25 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ተደርጎበት የመዋኛ ገንዳ፣ የስብሰባ አዳራሽና መደብሮች ይገነቡለታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኃይሌ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ፣ ላንድ ማርክ ሆቴልን በመረከብ ሙሉ በሙሉ ዕድሳት በማድረግና አዲስ የመዋኛ ገንዳ፣ የጤና መጠበቂያና የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከሎችን (ጂም፣ ስቲምና ሳውና)፣ የስብሰባ አዳራሽና የልጆች መጫወቻ ቦታዎችን በመገንባት ለጎንደር ከተማ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለማቅረብ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ኃይሌ ሪዞርት ጎንደር 66 ቅንጡ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች፣ ባህላዊውን ጨምሮ አራት የመመገቢያ አዳራሾች፣ ከ40 እስከ 500 እንግዶችን የሚያስተናግዱ አራት አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የዋና ገንዳ፣ ጤና መጠበቂያ የልጆች መጫወቻ ቦታዎችን፣ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ሱቆች ከበቂ የመኪና ማቆሚያ ጋር በማዋሃድ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ሪዞርቱ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ሲጀመር ከ200 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከጎንደር ባሻገር በሰሜን ተራሮች፣ በባህር ዳር፣ በላሊበላ፣ በአክሱም ተደራሽነቱን በማስፋፋት እንዲሁም በደብረ ብርሃን፣ በወላይታ ሶዶና በኮንሶ ለሆቴል ግንባታ መሬት ተረክቦ ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

‹‹ይህችን የመሰለች አገር ይዘን አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ቱሪስት ብቻ የምትስተናግድበት ታሪክ መለወጥ አለበት፤›› ያለው ኃይሌ፣ እንደ ግብፅ ያሉት አገሮች 20 ሚሊዮን ቱሪስቶች እንደሚያስተናግዱም በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡

የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያድግ ከተፈለገ ሁሉም የየበኩሉን መወጣበት እንዳለበት አስታውቆ በተለይም የፀጥታው ጉዳይ ሊታስብበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ከእስካሁኑም ይልቅ የወደፊቱ ሁኔታ እንደሚያሳስበው በመግለጽ የአገሪቱ የፀጥታ ችግሮች መላ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

አለመረጋጋቱ በተለይም ለቱሪዝምና ለሆቴል ዘርፉ ፈተና እንደሆነ የጠቀሰው አትሌት ኃይሌ፣ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚገታበት ወቅት ቱሪዝሙ አደጋ እንደሚያጠላበት አብራርቷል፡፡

‹‹ሐዋሳ ስንከፍት ሰው ቤተሰቡን፣ ጓደኛውን ይዞ ነው የሄደው፡፡ ኅብረተሰቡ ካልተንቀሳቀሰ ኢንዱስትሪውም ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ኢኮኖሚም ይጎዳል፤›› ብሏል፡፡

ከውጭ የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር መጨመር እንዳለበት በመጠቆምም ለቱሪስት ፍሰቱ እንቅፋት የሆኑ ቢሮክራሲዎች መሰበር እንዳለባቸው፣ ለአፍሪካውያን የመዳረሻ ቪዛ መፈቀዱም ለዘርፉ መልካም ለውጥ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

ኃይሌ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ከአራት ወራት በፊት በአርባ ምንጭ ከተማ ከከፈተው ኃይሌ ሪዞርት አርባ ምንጭ ባለአራት ኮከብ ሆቴል በተጨማሪ፣ ኃይሌ ሪዞርት ሐዋሳ (አራት ኮከብ)፣ ኃይሌ ሆቴል ሻሸመኔ (ሦስት ኮከብ)፣ ኃይሌ ሪዞርት ዝዋይ (ሦስት ኮከብ) እንዲሁም ያያ ቪሌጅ ይገኙበታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ባለአምስት ኮከብና በአዳማ ባለአራት ኮከብ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን ግንባታ በቅርቡ በማጠናቀቅ ለሥራ እንደሚያበቃቸው ይጠበቃሉ፡፡ የጎንደሩ ኃይሌ ሪዞርትም ወደ አራት ኮከብነት የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ኃይሌ ገልጿል፡፡

Source: The Reporter

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.