አንጌላ ሜርክል በፓርቲ ሊቀ መንበርነታቸው እንደማይቀጥሉ አስታወቁ

0

የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በፓርቲ ሊቀ መንበርነታቸው መቀጠል እንደማይፈልጉ አስታወቁ።

ሜርክል ፓርቲያቸው ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በታህሳስ ወር በሚያደርገው የሊቀ መንበርነት ምርጫ በድጋሚ የመመረጥና በሊቀ መንበርነታቸው የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ለፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ነግረዋቸዋል እየተባለ ነው።

የሜርክል ውሳኔ ፓርቲያቸው በሳምንቱ መጨረሻ በተደረገ የአካባቢ ምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ የመጣ ነው ተብሏል።

ሜርክል ከሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበርነታቸው ቢለቁም፥ በጀርመን መራሂተ መንግስትነታቸው ግን የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት ሜርክል የስልጣን ጊዜያቸው እስከሚያበቃበት የፈረንጆቹ 2021 ድረስ መራሂተ መንግስት ሆነው የሚቆዩ ሲሆን፥ ከ2021 በኋላ ስልጣናቸውን የሚለቁ ይሆናል።

ይሁን እንጅ ከፓርቲ ሊቀ መንበርነታቸው ለቀው በሃገር መሪነት የመቀጠላቸው ጉዳይ ጥያቄን እያስነሳ ይገኛል።

ውሳኔውን ተከትሎም ፓርቲያቸው የእርሳቸውን ምትክ ያፈላልጋል እየተባለ ነው።

አሁን ላይ የእርሳቸውን ውሳኔ ተከትሎም የጤና ሚኒስትሩ ዬንስ ስፋን፣ አርሚን ላሸት፣ አኔግሬት ክራምፕ ካሬንባወር እርሳቸውን ለመተካት ይወዳደራሉ እየተባለ ነው።

ከዚህ ባለፈም በፓርላማ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የቀድሞ መሪ ፍሪድሪክ ሜርዝ ከሜርክል ውሳኔ በኋላ ፓርቲውን በሊቀ መንበርነት ለመምራት በሚደረግ ምርጫ እሳተፋለሁ ብለዋል።

አንጌላ ሜርክል ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ ሃገራቸውን እየመሩ ሲሆን፥ አሁን ላይ በስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ የነበራቸው ተቀባይነት እየተሸረሸረ ስለመምጣቱ ይነገራል።

ለዚህ ደግሞ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ የሚከተሉት ፖሊሲ የጀርመናውያንን ደህንነትና ነጻነት የሚጋፋ ነው በሚል ጀርመናውያን ይተቻሉ።

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.