በዲላ ከተማ በኤሌክቲርክ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት አለፈ

0

በዲላ ከተማ በደረሰ የኤሌክቲርክ አደጋ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ምክትል ሳጅን ጴጥሮስ ዘለቀ እንደገለጹት፥ አደጋው ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 17 2011 ዓ.ም ከሌሊቱ 5 ሰዓት ገደማ ነው የደረሰው።

አደጋውም በዲላ ከተማ በተለምዶ ሞላ ጎልጃ ሰፈር ከሚባለው የከተማው ክፍል ወረድ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ነው የደረሰው።

በኤሌክትሪክ አደጋውም ወላጅ እናትን ጨምሮ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ በድምሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል።

ሌላ አንድ የቤተሰብ አባል በኤሌክትሪክ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ርፈራል ሆስፒታል ጽኑ ህሙማን ክፍል እርዳታ እየተደረገላት መሆኑንም አብራርተዋል።

አደጋው የደረሰውም ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተገናኘ የልብስ ማስጫ ላይ የተሰጣ ልብስ ለማስገባት ሲባል መሆኑን ምክትል ሳጅን ጴጥሮስ ዘለቀ አስታውቀዋል።

ህብረተሰብ ከኤለክትርክ መስመር ጋር ተያይዘው ያሉ ነገሮች ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውን የጌዲኦ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

Via FBC

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.