በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደየቀዬአቸው መመለሱ እንደሚያሳስባቸው ገለጹ

0

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በተለይ በምስራቅ እንዲሁም ደግሞ በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተጠለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሰላሙ ጉዳይ አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ ወደየቀዬአቸው መመለስ እንደሚያሳስባቸው ገለጹ፡፡
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተጠለሉት እነዚህ ተፈናቃዮች በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በነበሩበት አካባቢ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት በመከሰቱ ራሳቸውንና ልጆቻቸውን ለማዳን ሲሉ ሸሽተዋል፡፡ ቤት ንብረታቸውን በመጣል ቀዬአቸውን ትተው የመጡትም ሰላም ፍለጋ ነው፡፡
ይህ ሰላም ትተውት የመጡበት አካባቢ የማይሰፍን ከሆነ ግን ወደሥፍራው መመለስን አይሹም፡፡
ወይዘሮ ደራርቱ አብደላ እና ወይዘሮ ሰኬይና አብዱራሃማን በየበኩላቸው እንደገለጹት፤ የተፈናቀሉት ከሳሲጋ አካባቢ ነው፡፡ አሁን ባሉበት ሁኔታ መቀጠል ስለማይችሉ መንግሥት ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሁለቱም የልጆች እናት እንደመሆናቸው ወደሥፍራው የመመለሱ ጉዳይ ከስጋታቸው የተነሳ ልጆቻቸው ስለማይፈልጉት የእነርሱም ምርጫ አይደለም፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከገቡ በኋላ ግን የምስራቅ ወለጋ ህዝብና የአካባቢው ወጣቶች (ቄሮዎች) ያደረጉት ቁም ነገር ከፍ ያለ ነው፡፡
የሦስት ልጆች አባት የሆነው ወጣት ታደለ አስናቀው በበኩሉ፣ ተፈናቅሎ የመጣው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ከምትገኘው ሶጌ አካባቢ መሆኑን ጠቅሶ፣ግጭቱ ሲከሰት ጫካ ገብተው ስለነበር እዛው ጫካ ውስጥ ሦስት ቀን ማደራቸውን ተናግሯል፡፡ በሽሽታቸው ወቅት ወንዙ ሞልቶ ስለነበርም የያዟቸውን ህጻናት ያሻገሩት በዋና እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ወደዚህ ከመጣን በኋላ ግን ቄሮ ነው ነፍሳችንን ያዳነን፤ አሁን ግን ወደዛ ሥፍራ ተመልሶ መሄድ ያሰጋናል፡፡ ሰላም ወዳለበት ነው መሄድ የምንፈልገው›› ሲል ጠቅሷል፡፡
ከመዳ ጃለላ አካባቢ የተፈናቀሉት የሰባት ልጆች አባት አቶ ኑረዲን ሽመልስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በግጭቱ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ መሆኑ ባለመቻላቸው ተበታትነዋል፡፡ ሰላም ከሌለ ተመልሶ የመሄዱ ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ መንግሥት ከተፈናቃዮች ጎን መቆም አለበት፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን ጋሮማ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ከመስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በተፈጠረው ግጭት አማካይነት ተፈናቃዮች ወደ ነቀምት ከተማ የገቡ ሲሆን፣ዩኒቨርሲቲው ከአራት ሺ በላይ ተፈናቃዮችን አስጠልሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ወደ ጊቢው ተፈናቃዮች ከመምጣታቸው አስቀድሞ የፍራሽ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የተፈናቃዩ ቁጥር እየበዛ ሲመጣ ደግሞ ወደ 200 ያህል ብቻ የመቀበል ሃሳብ ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ከብዛቱ የተነሳ ግን በአንዴ ወደ አራት ሺ ተፈናቃዮችን ጊቢው በማስተናገድ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዶክተሩ እንዳሉት፣ዩኒቨርሲቲው በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው ሥራ ከማህበረሰቡ ጋር መነጋገር ሲሆን፣ የተለያዩ ኮሚቴዎችን አዋቅሯል፡፡ ጤናም አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ጉዳዩን የሚከታተል አንድ ግብረ ኃይል እንዲሁም ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰራም ኮሚቴ አዋቅሯል፡፡
እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከተፈናቃዩ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ሌሎች አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ልብስና ፍራሽን ጨምሮ አሁንም ድጋፍ እንደሚያሻ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ከደመወዙ 50 በመቶ ያህሉን ለመቁረጥ መስማማቱን ጠቁመዋል፡፡
እርሳቸው እንደገለጹት፣የዩኒቨርሲቲው ነባርና መደበኛ ተማሪዎች ጥቅምት አምስትና ስድስት ቀን 2011 ዓ.ም ተጠርተው ነበር፣ይሁንና አሁን ላልታወቀ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ይሆን ተብሎ ለተነሳው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን ከግምት በማስገባት የወሰነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በቅርቡ ግን ቀኑ የሚወሰን ሲሆን፣ በግቢው ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮችም ለጊዜያዊ መጠለያነት እንጂ እስከወዲያኛው በጊቢው የማይኖሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሁኔታዎች ከተመቻቹም በቀጣይ ሳምንት ከከተማ አስተዳደርና ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ከግቢው የሚለቁበት ሁኔታ አሊያም ወደመጡበት እንዲመለሱ የሚመቻች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ብቻ ተፈናቃዮች የመማሪያ ተቋማትን ጨምሮ በዘጠኝ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ መሆኑ ታውቋል፡፡

Via አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.