11ኛው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአደባባይ አይከበርም

0

11ኛው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአደባባይ እንደማይከበር የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል አከባበር ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ በዓሉ በብሄራዊ ደረጃ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚከበር ገልጿል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ 11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት በተቋማት ደረጃ በውይይት እየተከበረ ሲሆን፣የማጠቃለያው በዓል ግን እንዳለፉት ዓመታት በአደባባይ አይከበርም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ በሀገራችን አንዳንድ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ መሆናቸውን አምባሳደር መስፍን ጠቅሰው፣በዓሉ በአደባባይ የማይከበረው ይህን ግጭት ለማስቀረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹በዓሉን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ የማክበሩ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችለው ሥራ እስከሚከናወን ድረስ ከአደባባይ አለማክበሩ ይመረጣል በሚል ብሄራዊ ኮሚቴው በተስማማበት መሰረት በዓሉ ከአደባባይ ይልቅ በብሄራዊ ደረጃ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል›› ብለዋል፡፡
‹‹ሥራ ላይ ባለው ህገመንግስት መሰረት ሥራ ላይ ያለውን ሰንደቅ ዓላማ በበዓሉ ላይ ለማውለብለብ እንዲቻል የሚመለከተው አካል ሁሉ ግንዛቤ ሊጨብጥ ይገባል›› ሲሉም አምባሳደር መስፍን አስገንዝበዋል።
እንደ አምባሳደር መስፍን ማብራሪያ ፤ በዓሉ በተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ የሀገሪቱ አመራሮች ባሉበት በሰንደቅ ዓላማ መስቀል መርሀ ግብር የሚከበር ሲሆን፣ ይህም በተመሳሳይ ሰዓት በሁሉም አካባቢዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡በክልልም በፌዴራልም ደረጃ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ፣ ፖሊስ ፣በፌዴራልና በክልል የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ ሰዓት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ የሚያከብሩትም ይሆናል፡፡
በዓሉ በሰንደቅ ዓላማችን ስር ሆነን ለውጡን ለማስቀጠል ፣ልማታችንንና ዴሞክራሲያችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ቃል የምንገባበት ነው ያሉት ሰብሳቢው፣ ባንዲራው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አባቶችም ይሁኑ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ በየደረጃው ለሚከበረው በዓል ሁሉም የመንግሥት ተቋማት መገናኛ ብዙሃን፣ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሚውለበለበው ሰንደቅ አላማም በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ህገመንግሥት የሚያውቀው ሰንደቅ ዓላማ ነው ያሉት ሰብሳቢው፣ ‹በሰንደቅ ዓላማው ላይ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ይህንንም በተፈጠረው የለውጥ ጉዞ ፣የዴሞክራሲ ምህዳርን የማስፋት እንቅስቃሴ ፣ በህገመንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ በተቀመጠው ህጋዊ ማዕቀፍ በየደረጃው ለማስተካከል የሚፈለጉ ሀሳቦች ካሉ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ እነዚህን ተቀብሎ ለመወያየት እና አስተያየት ለመቀበል ወደፊት ሰፋፊ መድረኮች እንደሚያስፈልጉ የሚታመን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በለውጡ ጉዞ ውስጥና ሥራ ላይ ባለው ህገመንግስት መሰረት ለሰንደቅ ዓላማችን ሁሉም ወገን በዕለቱ ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

Via አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.