ብአዴን የተለያዩ ጥፋት የፈፀሙ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገለፀ

0

ዛሬም ቀጥሎ የዋለው የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የህግ የበላይነት፣ የማንነት፣ የወሰንና ድንበር ጥያቄዎች እንዲሁም በማዕከላዊ ኮሚቴ የታገዱ አመራሮች ጉዳይ ላይ በዋናነት መክሯል

የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ ምግባሩ ከበደ በሰጡት መግለጫ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አባላት ባለፉት ሶስት ዓመታት የክልሉን ህዝብ የበደሉ፣ ሀላፊነታቸውን አለአግባብ የተጠቀሙ አመራሮችን ስም እየጠቀሰ ጥፋታቸውን እያነሳ ጉባኤተኛው ትችት መሰንዘሩን ተናግረዋል።

ትችቱ ከፍተኛ ጥፋት ያለባቸውን አመራሮች የለየ እና መለስተኛ ጥፋት የፈፀመውንም በድርጊቱ ልክ ያስቀመጠ እንዲሁም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጥፋት የፈፀሙ አመራሮችን ያመላከተ እንደሆነ አቶ ምግባሩ ገልፀዋል። ከዚህም በመነሳት ጉባኤው ከአባልነት የሚያሰናብታቸው፣ ከአመራርነት የሚያወርዳቸው እና ሌሎች ፖለቲካዊ እርምጃዎችን የሚወስድባቸው የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የዚህ እርምጃ ዝርዝርም በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደሚገለፅ ነው ያመለከቱት። በክልሉ የህግ የበላይነትን የጣሱ በርካታ ድርጊቶች መፈፀማቸውንም ጉባኤተኞቹ እንዳነሱ ተናግረዋል። ድርጅቱም ሆኑ የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ሊያስከብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምርቶች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግዱ ህገወጥ ድርጊቶች በመፈፀማቸው በነጋዴውና በአርሶ አደሩ ህይወት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩንም ጉባኤተኞቹ አንስተዋል። በመሆኑም ህግን ማስከበር የዴሞክራሲ አንዱ ገፅታ ሆኖ እንዲተገበር ጉባኤተኞቹ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር ጉዳይ እስካሁን ድረስ እልባት ሳያገኝ መቆየቱ ስህተት እንደሆነም ጉባኤተኞቹ አስንተዋል። የድንበር ማካለሉ ጉዳይ የብአዴን ቀዳሚ ስራ ሆኖ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ነው የጠየቁት። በምእራብ ጎንደር የሚገኘው ደላሎ የተባለው አካባቢ ያለው መሬት ለሱዳን መሰጠቱ አግባብ አይደለም፤ ሊመለስ ይገባል ብለዋል።

የማንነት ጥያቄዎችንም በሚመለከት ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ በአፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከጉባኤተኛው ቀርበዋል። ከአሁን ቀደም የብአዴን ማዕክላዊ ኮሚቴ ከአባልነት ያገዳቸው አመራሮችን በተመለከተ የታገዱበት ምክንያት ለጉባኤተኞቹ ቀርቦ ክርክር ተደርጓል። ጉባኤተኞቹም ከታገዱት አመራሮች መካከል የጥረት አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ጥረትን በሚገባው ልክ ትርፋማ አላደረጉም እና ከብክነት አልታደጉም አሁን ያለው የጥረት ትርፍ ሊጣራ ይገባል የሚል ጥያቄንም ጉባኤተኞቹ አቅርበዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የጥረት አመራሮች ለጉባኤተኞቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጉባኤው ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፥ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ እስከዚህኛው ጉባኤ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታግደው የነበሩ አመራሮች በጉባኤው ላይ እንዲገኙ ጥሪ ተቀብለው አልተገኙም የተገኙትም ከአባልነት የታገዱበት ምክንያት አሳማኝና ፍትሃዊ እንዳልሆነ ለጉባኤው አስረድተዋል።

ጉባኤው በነገው ውሎ ከጉባኤተኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች በድርጅቱና በክልሉ ከፍትኛ አመራሮች ምላሽ የሚሰጥባቸው ሲሆን፥ የጉባኤው ረቂቅ ሪፖርትም ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Via FBC

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.