በ345 ሚሊየን ዶላር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የመንገደኞች ተርሚናል ግንባታ በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

0

በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የመንገደኞቸ ማስተናገጃ እየተካሄደ የሚገኘው የማስፋፊያ ግንባታ በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በጠቅላላው 345 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠየቀው የመንገደኛ ማስተናገጃ ግንባታ ከሶስት ወራት በኋላ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል።

የመንገደኛ ማስተናገጃው በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አየር መንገዱ የሚያስገነባውን ባለአምስት ኮኮብ ዓለም አቀፍ ሆቴል ጨምሮ የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ጎብኝተዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የመንገደኞች ማስተናገጃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 83 በመቶ ተጠናቋል።

የመንገደኞች ማስተናገጃው ግንባታ በምዕራብና በምስራቅ ሁለት አቅጣጫዎች ተከፍሎ እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በምስራቅ በኩል ያለው የተጠናቀቀ በመሆኑ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ቀሪው ሥራ በሦስት ወር ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።

ነባሩ የመንገደኞች ማስተናገጃ ያለው አቅም አምስት ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ቢሆንም እየሰጠ ያለው ግን ከ11 ሚሊዮን ለሚልቅ ተገልጋይ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።

ይህም ከፍተኛ መጨናነቅን ከመፍጠር ባሻገር በመንገደኞች ላይ እንግልት በመፍጠር ላይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አዲሶቹ ግንባታዎች የመንገደኞችን መጨናነቅና እንግልት ያስቀራል ብለዋል።

ማስተናገጃው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የገበያ፣ የመዝናኛና ምግብ ቤቶችና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎት መስጫዎች ይኖሩታል ተብሏል።

Via FBC

Share.

About Author

Ethio Newsflash is all about news stories from Ethiopia and beyond!

Comments are closed.